Wednesday, August 15, 2012

የእሳት ትንታግ ፍንጣሪ



የእሳት ትንታግ ፍንጣሪ
የድል ዜማ ወገን አኩሪ
የክብር ጥግ ማማ
የደስታ ውበት ቄጤማ
የመስቀሉን ኃይል ከግሸን የጸበሉን በረከት ዘግና
ይኽው አየኋ በለንደን የእሳት ልጅ እሳት ሆና
የደም አዙሪት ምሬቱ
የእሳት ትግል ሽረቱ
እየፈላባት ሐሞቷ እየታገላት ሲቃ
ታቦቷን ከራሷ ሳይሆን ከደረቷ ላይ ደብቃ
ተሻገረችው ያንን ጉድ አስለቀሰችን ነፍርቃ
ጀመረች አግዥኝ ብላ
ድንግልን በደረቷ አዝላ
ታሪክ ናት ይኽች ማሪያም ለተማጸናት በብርቱ
ልጇን ላመነ በልቡ ፍቅሯን ላሰረ በአንገቱ
እረሳችና ድካሟን የልፋት ውጤት ወርቋን
ከፍ አደረገችው ስእሏን የድንግል ማርያምን ስሟን
ግሸን ሆነች አሉ ለንደን ተቀይራ
መሰረተ ህይወት ድንግል ተዘምራ
እምነት ከጉያ ውስጥ ድንገት ፈለቀና
ሃሌ ሃሌ ሆነ ድካም ተረሳና
የእኛ ርግብ አማኝቷ
የኢትዮጵያ ልጅ መሠረቷ
ቢላላባት ያሰረችው ቢበጣጠስ መቀነቷ
ተወራርዳ አሸነፈች በጌታ እናት ባዛኝቷ

መ/ር አቡኑ ማሞ
ዋሽንግተን ዲሲ

No comments:

Post a Comment