(ኤፍሬም እሸቴ- በግል)
(READ IN PDF):- ማክሰኞ ሚያዚያ 9/2004 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ እንደተለመደው የምክር ቤቱ ክቡራን አባላት በንባብ ላቀረቡላቸው ጥያቄዎቻቸው መልስ ሲሰጡ ተከታትያለኹ። ከጥያቄዎቹ አንዱ ወቅታዊው የሙስሊሞች ጉዳይ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው “መንግሥት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ አልገባም” የሚለውን በሰፊው ሲያብራሩ ቆዩ። አንዱ ማብራሪያቸው ስለ ሰላፊያዎች (አል-ሰላፊያ ወይም ወሐቢያዎች) ነው። ራሳቸውን “አል-ሰላፊዩን” የሚሉትና ትክክለኛውን የቁርዓን ትምህርት እንከተላለን የሚሉት የሙስሊም ክፍል የሆኑትና መሠረታቸውን በሳዑዲት አረቢያ ያደረጉት ጽንፈኛ ወገኖች በተቃዋሚዎቻቸው ደግሞ “ወሐቢያዎች” ይባላሉ። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ወሐቢያዎች እና ስለአክራሪነታቸው ማተት ስላልሆነ የዚህን ቡድን አስተምህሮ እና በኢትዮጵያ ላይ ስለ ጋረጠው ከፍ ያለ አደጋ “አክራሪ እስልምና በኢትዮጵያ” (ኤፍሬም እሸቴ፣ በ2000 ዓ.ም/ 2008 የታተመ) የሚለውን መጽሐፍ ማንበብ እንደሚቻል በመጠቆም አልፋለኹ።
ወደ ርዕሰ ጉዳያችን ስንመለስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ሙስሊም አክራሪዎች ከማብራራታቸው ጎን ለጎን ደግሞ አክራሪነት በእስልምና ብቻ ያልተገታ መሆኑን ለማስረዳት በሚመስል መልኩ በክርስትናው ውስጥ በተለይም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለውን በምሳሌነት ለማንሣት በጥምቀት ወቅት ወጣቶች ይዘውት ወጡ ያሉትን መፈክር ጠቅሰዋል። “ጥምቀት ላይ ከነበሩት መፈክሮች አንዱ ‘አንድ አገር - አንድ ሃይማኖት’ የሚል ነው። …. ‘አንድ አገር - አንድ ሃይማኖት’ የሚል ሕገ መንግሥት የለንም። (መፈክሩ) … የክርስቲያን መንግሥት እንዲኖር የሚፈልጉ … እንዳሉ ያሳየናል” ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ።“የዚህም መነሻው የግንዛቤ ማነሥ በመሆኑ በማስተማር የሚመለሱ ናቸው” ሲሉ አክለዋል።
ቀጥለውም ይኸው አክራሪነት በክርስትናም ውስጥ እየታየ መሆኑን ለአብነትም ጥምቀት ላይ የሚታዩ መፈክሮችን ካብራሩ በኋላ አክራሪዎቹ “አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የሚያራምዱትን ግልባጭ ሲያራምዱ ታይተዋል” ሲሉ የእስልምናው “ሰለፊ” በክርስትናው በተለይም በኦርቶዶክሱ በኩል “ማኅበረ ቅዱሳን” ነው የሚል አንድምታ ያለው አጭር ነገር ግን ከባድ ኃይለ ቃል ተናግረው አልፈዋል። “አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የሚያራምዱት” ያሉት ግን ምን መሆኑን በርግጥ አላብራሩም። ምናልባት ከላይ “አንድ አገር - አንድ ሃይማኖት” የሚል መፈክር ያዙ የተባሉት የጥምቀት አክባሪዎች “የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ሳይሆኑ አይቀሩም/ ናቸው” በሚል እሳቤ የተናገሩትም ይመስላል። ወደ ኋላ እንመለስበታለን።
በመጀመሪያ “አንድ ሃይማኖት” የሚለው መሠረታዊ ሐሳብ ለብዙ ውይይቶች በር የሚከፍት ትልቅ ጉዳይ ነው። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚያስተምረን እና የጥምቀት አክባሪ ክርስቲያኖች በቲ-ሸርቶቻቸው ላይ አትመውት በፎቶግራፍ የተመለከትኩት ኃይለ ቃል ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ ምዕራፍ 4 ቁጥር 5ላይ የጻፈው “አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት” የሚለው ሐዋርያዊ ቃል ነው። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል እንጂ የጥምቀት አክባሪዎቹ የፈለሰፉት አይደለም። በዚህ የሐዋርያው ቃል ውስጥ ያለው “አንድ ሃይማኖት” የሚለው አገላለጽ የሚናገረው ስለ ክርስትና ሃይማኖት ነው። ሌሎች እምነቶች የሉም፣ መኖርም የለባቸው የሚል የጨፍላቂነት ትምህርት አለመሆኑን ሊቃውንቱ አምልተው አስፍተው ሲያስተምሩ ኖረዋል፤ እያስተማሩም ነው።አሁን ደርሶ የሚለወጥ ነገር የለም።
በኢትዮጵያ ዐውድ ከተመለከትነው “ክርስቲያኖች ኢትዮጵያ የምትባለው አገር የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ብ….ቻ ናት፣ ያለ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሌሎቻችሁ ቦታ የላችሁም ትላላችሁ” የሚል አንድምታ እየሰጡ የሚናገሩ እና የሚጽፉ ብዙ ኢትዮጵያውያን ከመኖራቸው አንጻር “አንድ ሃይማኖት” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል አንዳንድ ሰዎች የተሳሳተ ትርጉም እንዳለው አድርገው እየተጠቀሙበት እንዳይሆን ሥጋት አለኝ።
“አንድ ሃይማኖት” የሚለው አገላለጽ ከሃይማኖት ጋር በማይተዋወቁ ሰዎች ዓይን ከተመለከትነው መቻቻልን ለማስተናገድ ፈቃደኝነት የጎደለው አገላለጽ ሊመስል ይችላል። መቻቻል ማለት ግን መሠረታዊ የራስን ሃይማኖት አስተምህሮ መናድና መካድ ስላልሆነ መፍትሔው እርስ-በርስ መገነዛዘብና መረዳዳት ነው። የትኛውም ክርስቲያን “አንድ ሃይማኖት” ቢል የሐዋርያውን ቃል መጥቀሱ እንጂ ሌላ እምነት ላላቸው ኢትዮጵያውያን ጥላቻ አለው ማለት አይደለም። የጥምቀት አክባሪ ወጣቶች ቲ-ሸርቶች ላይ የተጻፈውን የሐዋርያውን ቃል የምረዳው በዚህ መንፈስ ነው።
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት መፈክር “አንድ ሃይማኖት” ብቻ ብሎ ሳያበቃ “አንድ አገር” የሚለውን ጨምሮበት “አንድ አገር - አንድ ሃይማኖት” በሚል ተጽፎ ከሆነ አባባሉ ሌላ ትርጉም ማለትም “የክርስቲያን መንግሥት ለመመሥረት መሻት” የሚል አንድምታ ሊሰጠው ይችላል። ቲ-ሸርቶችን የለበሱ እና ባነሮችን የያዙ ወጣቶች በጥምቀት በዓላት አሁን ባለው መልክ በዓል ማክበር ከጀመሩ ገና ሁለት ወይም ሦስት ዓመታቸው ነው። በነዚህ ሁለት ወይም ሦስት ዓመታት የጥምቀት በዓላት ላይ የተነሱ እና ከተለያዩ ድረ ገጾችና ማኅበራዊ ገጾች የሰበሰብኳቸውን ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ፎቶግራፎችበድጋሚ በጥንቃቄ ለመመልከት ሞክሬያለኹ። እነዚህ በተለያዩ ካሜራዎች፣ በተለያዩ አንሺዎች፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎችና በተለያዩ ቦታዎች ከተነሡት ፎቶግራፎች ውስጥ ጠ/ሚኒስትሩ ያሉትን ዓይነት ጥቅስ ወይም ተመሳሳዩን ፈልጌ ላገኝ አልቻልኩም። በርግጥ መፈክሩ በነዚህ ፎቶዎች ውስጥ ባለመገኘቱ የተነገረው ነገር ስህተት ነው ማለት ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ከመፈክሩ ከባድነት እና ከያዘውም ሐሳብ ጽኑዕነት አንጻር አንዱም ፎቶ አንሺ ሊያነሳው ያለመቻሉ ሁኔታ የአጋጣሚ ብቻ ነበር ለማለት አያስችልም። ስለዚህ አስቀድሞም ኅሊናዬ እንደሚነግረኝ እንዲህ የሚል ጥቅስ አልነበረምም አልተጻፈምም ለማለት እደፍራለኹ።
“አንድ አገር” የሚለውን ነጥብም በተመለከተ ባለሙያዎች የበለጠ ሊያብራሩት እንደሚችሉ ባምንም በግሌ የሚሰማኝን ግን በአጭሩ ለመጠቆም እሞክራለኹ። እዚህ በምንኖርበት አገር በአሜሪካ Pledge of Allegiance የሚሉትና ቃል ኪዳናቸውን የሚያጸኑበት መሐላ (ማለትም "I pledge allegiance to the flag of the United States of America, and to the republic for which it stands, one nation under God, indivisible, with liberty and justice for all”) አላቸው። አሜሪካዊ የሆነ ሁሉ ከትንንሽ ተማሪዎች እስከ ምክር ቤት አባላት ድረስ ያውቁታል፣ በየአጋጣሚውም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይሉታል። ለአገራቸው ያላቸውንም ቃል ኪዳን ይገልፁበታል።
አንድ አገር/ one nation under God ያሉት ግን የሁሉም የሆነ አገር ማለታቸው መሆኑ ግልጽ ነው። አገር የጥቂቶች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ሊሆን ይገባዋል። ኢትዮጵያን በምሳሌነት ካነሣን በአንዲቱ አገራችን ውስጥ ኢትዮጵያውያን ለብዙ ሺህ ዓመታት በሰላም እንደኖርነው ሁሉ አሁንም ክርስቲያኑም፣ ሙስሊሙም፣ የሚያምነውም የማያምነውም “አገሬ” ብሎ ሊኖርባት ይገባል እንጂ ለዚህኛው እምነት ተከታይ “አገር” ሆና ለሌላው እምነት ተከታይ ደግሞ አገር የማትሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም።
“አንድ አገር” ሲባልም ሥጋት የሚገባው ዜጋ ሊኖር አይገባም። “አንዲት አገር” ዜጎቿ ተጨፍልቀው፣ ተጠፍጥፈው የምትፈጠር አይደለችም። በሌላ ጽሑፍ እንዳነሣኹት ኢትዮጵያውያን ብዙዎች ብንሆንም አንዲት አገር ናት ያለችን።አገራችን ቀለማችንና ቋንቋችን ለየቅል ቢሆንም ሁላችን በአንድነት የምንኖርባት የጋራ ቤታችን ናት። ኢትዮጵያውያንም እንደ አሜሪካኖቹ “ከፈጣሪ በታች ያለች አንዲት አገር/ one nation under God” አለችን ብንል የሚያሳፍር አይሆንም። በእርሷ ነውና እኛም “ኢትዮጵያውያን” የተባልነው። በሃይማኖትም አንጻር ካየነው ይህቺ አገራችን ቅዱሳን በኪደተ እግራቸው የባረኳት፣ አበው በደማቸው የጠበቋት፣ እምነት እና ቋንቋ ሳንለይ የምንኖርባት ቅድስት ምድር ናት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እግረ መንገዳቸውን ያነሱትን እና በኢትዮጵያ ውስጥያለውን “አክራሪነት” በክርስቲያኑ በኩል “ይወክልልናል” ብለው የጠቀሱትን ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ እኔም እንደ አንድ አባል የማምንበት አቀርባለኹ። ማኅበሩ በኃላፊዎቹ በኩል የሚሰጠው መልስ እንደተጠበቀ ሆኖ ለሁለት አሥር ዓመታት አባል የሆንኩበት እና መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በመስጠት በሁሉም ዘንድ የተመሰከረለት ማኅበር “አክራሪ” አለመሆኑን በግሌ ለመመስከር እገደዳለኹ።
ውድ ወንደሜ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን ተናገሩ ዶሮ ምን ለቀመች አይባልም፡፡ ብስልና ጥሬ፣ አሰስና ገሰስ ነውና፡፡ በቅርቡ የተናገሩትም በአብዛኛው ከዚያ የተለየ ነገር የለውም፡፡ ጥቂት እውነት ግን አለው፣ ማንንም አያንጽም እንጂ በማስረጃ መደገፍ ይቻላል፡፡ ወደ አንተ አስተያየት ስመለስ ግን ያው የእሳቸውን የመሰለ፣ በጭፍን ጥላቻ የተሞላ ነው፡፡ ደግሞ ምኑን ከምኑ አገናኘኸው፤ ነገርህ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ሆነ፡፡ የዛሬ 20 ዓመት ገደማ አንተና ማኅበርሕ በግፍ ያሳደዳችኋቸውን ክርስቲያኖች መድረሻ ለማሳጣት መአሕድ ናቸው፣ የፖለቲካ ዓላማ አላቸው ትሉ ነበር፤ ውሸታቸሁ ፀሐይ ሲሞቀው ተዋችሁት እንጂ፡፡ አሁንም ያው ናችሁ፣ በገዢውም ሆነ በተቃዋሚው ጎራ ብዙ ሰልፈኛ ያላቸሁ አንተና ማኅበርሕ ሆናቸሁ ሳላችሁ ወንጌል ለመስበክ ደፋ ቀና በሚሉት ወገኖችህ ላይ ፖለቲካዊ አፍህን ታላቅቃለህ፡፡ የሃገሬ ሰው እንደሚለው በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርምና እናንተም አክራሪ፣ አሸባሪ ተባላችሁ፡፡ ይኸው ነው፡፡
ReplyDelete