Saturday, April 7, 2012

ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ቅዳሜና እሑድ የመልስ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ




ቅዳሜና እሑድ ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫና ለአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የሚጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ዛሬና ከነገ በስቲያ ምሽት ወደ ቱኒዚያና ግብፅ ያመራሉ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ኢትዮጵያ ቡና ከሁለት ሳምንት በፊት ተጋጣሚዎቻቸውን በሜዳቸው አስተናግደው በአቻ ውጤት ማለትም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቱኒዚያው ክለብ አፍሪካ ጋር 1ለ1፣ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከግብፁ አልሃሊ ጋር 0ለ0 በሆነ ውጤት መለያየታቸው የስፖርት ቤተሰቡን ከማሳዘኑም በላይ ሁለቱም ቡድኖች ቅዳሜና እሑድ የሚያደርጉት ጨዋታ የውድድሩን መርሐ ግብር ለማሟላት ካልሆነ በውጤት ደረጃ ሁለቱም ቡድኖች ተስፋ እንደሌላቸው ይነገራል፡፡
ምክንያቱ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ኢትዮጵያ ቡና ሜዳቸው ላይ ባደረጉት ጨዋታ ቢያንስ ግብ አስቆጥረው ማሸነፍ ሲገባቸው ነገር ግን በተቃራኒው ተጋጣሚዎቻቸው ክለብ አፍሪካና አልሃሊ ከወትሮው በተለየ የተሻለ ተንቀሳቅሰው ውጤት አስጠብቀው መመለስ መቻላቸው በሜዳቸው ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን ዕድል ያመቻቸበት ሁኔታ የሰፋ በመሆኑ ነውም ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት በበርካታ የዓረብ አገሮች እየተስተዋለ የሚገኘው የሕዝብ አመፅ ቅዱስ ጊዮርጊስን በሚያስተናግደው ቱኒዚያ የተረጋጋ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ቡና የሚጓዝበት ግብፅ ግን አመፁ እንደቀጠለ ነው፡፡ አገሪቱን እያስተዳደረ የሚገኘው ጊዜያዊ መንግሥት የግብፅ ሕዝብ እግር ኳሱን ምክንያት አድርጐ መሰባሰብ እንዳይችል በአገሪቱ ምንም ዓይነት የሊግ ውድድር እንዳይካሔድ አግዷል፡፡ 
ሆኖም ግን አልሃሊና ዛማሊክ አገሪቱን በአፍሪካ መድረክ የወከሉ ክለቦች ከመሆናቸው የተነሣ በአገራቸው የሚያደርጉት ጨዋታ ተመልካች በማይኖርበት ዝግ ስታዲየም እንዲጫወቱ ውሳኔ ላይ መድረሱ ተነግሯል፡፡ 
ይህንኑ በሚመለከት የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ደስታ፣ የግብፅ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ሆነ ለኢትዮጵያ ቡና ያስተላለፈው መልዕክት፣ ከአልሃሊ ጋር የሚጫወተው ኢትዮጵያ ቡና በግብፅ አንዳች ችግር እንዳይገጥመው፣ እንዲያውም ቡድኑ የሚያርፍበት ሆቴል፣ ልምምድ የሚሠራበት ስታዲየምና ዋናውን ጨዋታ የሚያደርግበትን ስታዲየም ጭምር የትና በምን ሁኔታ መጠቀም እንደሚችል ያብራራበት ሁኔታ እንዳለ አስረድተዋል፡፡
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ያለተመልካች በዝግ ስታዲየም መከናወኑን በተመለከተ ግን ምንም ዓይነት መረጃ እንዳልደረሳቸው ነው የገለጹት፡፡

No comments:

Post a Comment