
ቅዳሜ ሚያዝያ ፳፪ ቀን ፲፰፻፷፰ ዓ.ም ከሸዋ ንጉሥ ምኒልክና ከወረኢሉ ተወላጅ ከወይዘሮ አብቺው በእነዋሪ ከተማ ተወለዱ።ሐምሌ ፲፩ ቀን ሰኞ ሥርዓተ ጥምቀት ተፈጽሞላቸው፣ የክርስትና ስማቸው አስካለ ማርያም ተባለ። ግርማዊት ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ለዳግማዊ ምኒልክ ሦስተኛ ልጅ ሲሆኑ ከልጅ ኢያሱ ቀጥለው መኳንንትና ሕዝቡ መክሮና ዘክሮ በምርጫ በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ የተቀመጡ ብቸኛዋ ንግሥት ናቸው።
አባታቸው የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ዳግማዊ ዐፄ) ዘውዲቱ የስድስት ዓመት ሕጻን እንደነበሩ ለአሥራ ሁለት ዓመቱ የዐፄ ዮሐንስ ልጅ ለአርአያ ሥላሴ ዳሩዋቸው። ጋብቻቸውም ጥቅምት ፲፫ ቀን ፲፰፻፸፭ ዓ.ም. በተክሊልና በቁርባን ተፈጸመ፡ የሠርጉም ማማርና የሽልማቱ ብዛት ሊነገር አይቻልም። ልጅ ኢያሱ መስከረም ፲፯ ቀን ፲፱፻፱ዓ.ም ከስልጣን ሲወርዱ፤ መኳንንቱና ሕዝቡ መክሮና ዘክሮ በምርጫ ወይዘሮ ዘውዲቱን ግርማዊት ንግሥተ ነገሥት፤ ራስ ተፈሪ መኮንንን አልጋ ወራሽ እና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ እንዲሆኑ ወስነው መስከረም ፳፩ ቀን "ግርማዊት ዘውዲቱ፣ ንግሥተ ነገሥት ዘኢትዮጵያ" ተብለው ነገሡ። በመኳንንቱም ምክር መሠረት ጳጳሱና እጨጌ ወልደጊዮርጊስ "ኢያሱን የተከተልክ፣ ያነገሥናትን ዘውዲቱንና ራስ ተፈሪን የከዳህ፣ ውግዝ ከመአርዮስ" እያሉ በአዋጅ አወገዙ፡:
ከዚህ በኋላ በጥቅምት የሰገሌ ጦርነት ከተደረገ በኋላ የዘውድ በዓሉ የካቲት ፬ ቀን ፲፱፻፱ ዓ.ም እንዲሆን ታዞ፣ ለዘውዱ በዓል በኢትዮጵያ አዋሳኝ ያሉት የእንግሊዝ ሱዳንናየእንግሊዝ ሱማሌ ገዥዎች፤ የፈረንሳይ ሱማሌ ገዥ እና በኢትዮጵያም ታላላቅ ራሶች እንዲሁም የየአውራጃው ገዥዎች በተገኙበት በዕለተ እሑድ አባታቸው ባሠሩት በትልቁ ደብር በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ ቅብዐ መንግስት ተቀብተው የንጉሠ ነገሥቱን ዘውድ ጫኑ። ከዚህም በኋላ እንደ ሥርዓተ ንግሡ ሕግ፤ ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ በአባታቸው ዙፋን ተቀምጠው መንገሣቸውን፤ ደጃዝማች ተፈሪም ራስ ተብለው አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ መሆናቸውን በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት አዋጅ ተነገረ።
የንግሥተ ነገሥታትን ሥልጣን ለማሳወቅ ሲባል ራስ ወልደ ጊዮርጊስ የካቲት ፲፩ ቀን ንጉሥ ወልደ ጊዮርጊስን ንጉሠ ጎንደር ብለው አንግሠው ዘውድ ደፉላቸው። እንደዚሁምመስከረም ፳፯ ቀን 1921 ዓ.ም. ብዙ መኳንንትና መሣፍንት፤ ሊቃውንትና ጳጳሳት ባሉበት የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንንን አዲስ አበባ መካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን፣ ንጉሥ ተፈሪ ተብለው ዘውድ ተጫነላቸው።
ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በነገሡ በአሥራ ሦሥት ዓመት ተኩል በ፶፬ ዓመት ዕድሜያቸው ረቡዕ መጋቢት ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፪ ዓ.ም በ ፰ ሰዓት ዐረፉ። የሞታቸው ዜና እንደተሰማም በከተማው የሐዘን ጥላ አጠላበት። አባታቸው ዐፄ ምኒልክ በተቀበሩበት በታዕካ ነገሥት በዓታ ቤተ ክርስቲያን ተቀበሩ።
No comments:
Post a Comment